የአለማችን የጤና ስጋት የሆነው ኮቪድ-19 በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይም በቂ መተዳደሪያ በሌላቸው፣ በአነስተኛ ስራዎች ላይ በተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ በአቅመ ደካሞችና የእድሜ ባለጸጎች ላይ ዘርፈ ብዙ ተጽእኖ ማስከተሉ ይታወቃል፡፡
የበሽታው ስርጭት ዛሬም በመጨመር ላይ ቢገኝም አስፈላጊ ጥንቃቄዎችን በማድረግ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ በተወሰነው መሰረት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤቶች መሄድ ጀምረዋል፡፡ በዚሁ መሰረት በደማቸው ውስጥ ቫይረሱ ያለባቸውና ድጋፍ የሚፈልጉ ተማሪዎች በትምህርት መሳሪያዎች እጦት ምክንያት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ በማሰብ የአርሲ ዩኒቨርሲቲ የኤችይቪ-ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ዳይሬክቶሬት ለ400 ተማሪዎች የአልባሳት፣ የደብተር፣ የእስክርቢቶና የእርሳስ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ዳይሬክቶሬቱ ድጋፉን ያደረገው ከዞኑ የቀይ መስቀል ማህበርና ከቀይ መስቀል በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ጋር በመተባበር ከተለያዩ ወገኖች በማሰባሰብ ነው፡፡