Wednesday, 14 October 2020 16:23

አርሲ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹን መልሶ ለመቀበል ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡

Written by
Rate this item
(0 votes)

የአለማችን የጤና ስጋት የሆነው ኮቪድ-19 መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም በአገራችን መታየቱን ተከትሎ የከፍትኛ ትምህርት ተማሪዎች ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ መወሰኑ ይታወቃል፡፡ በዚሁ መሠረት አርሲ ዩኒቨርሲቲ በሁሉም ካምፓሶቹ የሚገኙትን ተማሪዎች ከመጋቢት 16-17 ቀን 2012 ዓ. ም ቤተሰቦቻቸው ወደሚገኙባቸው አካባቢዎች ሸኝቷል፡፡ አርሲ ዩኒቨርሲቲ በራሱ እና በተከራያቸው ተሸከርካሪዎች ተማሪዎቹን ወደ ቤተሰቦቻቸው ከማድረሱም በላይ አውቶቡሶቹ ሲመለሱ ወደ አዲስ አባባ፣ አዳማ፣ አሰላና ባሌ-ሮቤ የሚጓዙ በተለያዩ ዩኒቨርሲዎች የሚማሩ ተማሪዎችን በማጓጓዝ ከወጪና ከእንግልት ታድጓቸዋል፡፡ አርሲ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ወደ ቤተሰቦቻቸው ለማጓጓዝ ከፍተኛ ወጪ ማውጣቱን በወቅቱ መግለጻችን ይታወሳል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎቹን ወደ ቤተሰቦቻቸው ከሸኘ በኋላ ከትምህርት እንዳይርቁና ከመምህራን ጋር በኦን ላይን እንዲገናኙ ለያንዳንዱ ተማሪ አዲሚኒስትሬሽን ፓስ ዎርድ በመስጠት ግንኙነታቸው እንዳይቋረጥ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ በዚህም የድህረ ምረቃ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በኦን ላይን አጠናቅቀው የመመረቂያ ጽሑፋቸውን በማዘጋጀት ተቋቁሞ (Oral Defence) አቅርበዋል፡፡

በአገራችን ዛሬም የኮቪድ-19 ስርጭት በመጨመር ላይ ቢገኝም መንግሥት አጠቃላይ ሁኔታውን በመገምገም በወረርሽኙ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የገጽ ለገጽ ትምህርት የወረርሽኙን ስርጭት የማያባብሱ የተለያዩ ሞዳሊቲዎችን በመጠቀም መልሰው እንዲከፈቱ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርም በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ከጥቅምት 2013 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ተቋርጦ የነበረውን ትምህርት ለመጀመር በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የትምህርትና ሥልጠና ተቋማትና የማኅበረሰብ መተዳደሪያ መመሪያ በማውጣት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተጨባጭ ያሉበትን ለመገምገም የኢንስፔክሽን ቡድን ወደ ዩኒቨርሲቲዎች አሰማርቷል፡፡ አርሲ ዩኒቨርሲቲም በቅድመ መልሶ ቅበላ የዝግጅት ምዕራፍ ያከናወናቸው ተግባራት በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የኢንስፔክሽን ቡድን ከመስከረም 24-25 ቀን 2013 ዓ.ም ለሁለት ቀናት ተገምግሟል፡፡ 

          የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የኢንስፔክሸን ቡድን የግምገማውን ሪፖርት ሲያቀርብ

በዚሁ መሠረት አርሲ ዩኒቨርሲቲም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተማሪዎችን መልሶ ለመቀበል መሟላት ያሉባቸውን መመዘኛዎች በመተግበር ተማሪዎችን መልሶ መቀበል የሚያስችሉትን ዝግጅቶች በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የኢንስፔክሽን ቡድኑም ዩኒቨርሲቲው በዝግጅት ምዕራፍ ተማሪዎችን መልሶ ለመቀበል ያከናወናቸውን ተግባራት በተዘጋጁ የግምገማ ነጥቦች ከገመገመ በኋላ የግምገማውን ውጤት በጥንካሬና መስተካከል ያለባቸውን (በክፍተት የታዩትን) በመለየት ሪፖርት አቅርቧል፡፡

          የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢና የአሰላ ከተማ ከንቲባ ስለተማሪዎች ቅበላ ለተሰብሳቢዎች ንግግር ሲያደርጉ

በቀረበው ሪፖርት መሰረት በዝግጅት ምዕራፍ አፈጻጸም መገምገሚያ መለኪያ መሰረት በጥንካሬ የታዩ፡-

 • የዩኒቨርሲቲው አመራርና የሰው ኃይል አደረጃጀትና ዝግጅት
 • በመማር ማስተማር በኩል በቂ የመሰረተ ልማትና አገልግሎት ዝግጅት መኖሩ
 • የሕግና እቅድ ማዕቀፎች መዘጋጀታቸው

በክፍተት የታዩ፡- በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ የበለጠ ሊሰራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች

 • የኮቪድ-19 መከላከልና መቆጣጠር ግብረ ኃይል የራሱን እቅድ በማውጣት ወደ ሥራ ማስገባት
 • ለኮቪድ-19 መከላከል ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ ግብአቶች እና የመሳሰሉትን ከተማሪዎች ቅበላ በፊት ገዝቶ ለሥራ ክፍሎችና ለኮሌጆች ማከፋፈል
 • በሁሉም የአገልግሎት መስጫ ቦታዎች የወንበሮችና የጠረጴዛዎችን ርቀቶች በአንድ ሜትር አራርቆ ማደራጀት
 • የግንዛቤ መፍጠሪያ በራሪ ወረቀቶችን ማዘጋጀትና ተደራሽ ማድረግ፤ በፖስተሮችና ባነሮች ትምህርታዊ የሆኑ መልዕክቶችንና ማስታወቂያዎችን ተደራሽ ማድረግ
 • ኮቪድ-19ን በመከላከልና በመቆጣጠር የመማር ማስተማሩንም ሆነ ሌሎች አስተዳደራዊ ሥራዎችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ማከናወን የሚያስችል ዕቅድ በማቀድ እስከ ታችኛው አመራርና ፈፃሚ አካላት ማውረድ

በተቋሙ የታዩ ምርጥ ተሞክሮዎች

 • ከንኪኪ ነፃ የሆነ የተማሪዎች ምዝገባ ማድረግ የሚያስችል የአይሲቲ መሰረት ልማት፤ የተሟላ የኔት ወርክ እና ኢንተርኔት አገልግሎት፤ የሴኩሪቲ ካሜራ፤ ተማሪዎች መምህራንና ተመራማሪዎች በመለየታቸው ገብተው ሊያገኟቸው የሚችሉ የኦን ላይን የቤተ መጽሃፍት አገልግሎቶች፤
 • የግቢ ንጽህና አያያዝና ለተቋሙ ማኅበረሰብና ተገልጋዮች ምቹና ጤናማ ጥሩ የሥራ መንፈስ የሚፈጥር ከባቢ የተፈጠረበት ሁኔታ
 • ከማኅበራት ጋር ያለው የሥራ ትስስርና ውጤታማነት እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው አድካሚ የሆኑ ዋናውን ተልዕኮ ለመተግበር እንቅፋት የሚሆኑ ሥራዎችን በመለየት የሰጠበትና እየታየ ያለው ውጤት ምርጥ ተሞክሮ ከሚሆኑት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

በመጨረሻም አርሲ ዩኒቨርሲቲ የሦሥተኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲ ቢሆንም ከዕድሜው በላይ በመሄድ በርካታ ሥራዎችን ማከናወኑን ማወቅ ተችሏል፡፡ አርሲ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በሶስት ዙር የሚቀበልበት ሁኔታ ሲታይ ከላይ በኢንስፔክሽን ቡድኑ እንደ መነሻ የታዩትን ክፍተቶች በመያዝ የተፈጠረውን አደረጃጀት እስከ ታችኛው ፈጻሚና አመራር በማውረድና ሁሉንም የተቋሙን ማህበረሰብ በንቅናቄ መልክ ወደ ስራ በማስገባት እንዲሁም ከላይ በዝርዝር በክፍተት የተነሱ ጉዳዮች በኮቪድ᎐19 ፕሮቶኮል መመሪያ መሰረት አናቦ መስራት ከተቻለ በመጀመሪያው ዙር ተመራቂ ተማሪዎችን መቀበል የሚችልበት የተሻለ አቅም ስላለው ከጥቅምት ሁለተኛ ሳምንት ጀምሮ መቀበል ይችላል በማለት የኢንስፔክሽን ቡድኑ የውሳኔ ሀሳብ አቅርቧል፡፡ አርሲ ዩኒቨርሲቲም በቅድመ ቅበላ ምዕራፍ ያላጠናቀቃቸውን ሥራዎች በማጠናቀቅ የተቋረጠውን ትምህርት መቀጠል እንደሚችል ተገልጿል፡፡

Read 841 times Last modified on Wednesday, 14 October 2020 16:33

Leave a comment

Make sure you enter all the required information, indicated by an asterisk (*). HTML code is not allowed.