Monday, 14 September 2020 17:15

አርሲ ዩኒቨርሲቲ የምስጋና ቀን አከበረ፡፡

Written by
Rate this item
(3 votes)

አርሲ ዩኒቨርሲቲ ራዕዩን በማሳካት የተጣለበትን አገራዊ ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት እና ስትራቴጂያዊ እቅዶቹን እውን ማድረግ እንዲችል ከተለያዩ መንግሥታዊ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ ድርጅቶች እና ታዋቂ ግለሰቦች ጋር በቅንጅት ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በሁሉም መስክ የላቀ ውጤት ማስመዝገብ የቻለው ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራቱና እነዚህ አካላት ከጎኑ በመሰለፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስላበረከቱለት መሆኑን በመገንዘብ ደጋፍ ያደረጉለትን አካላት አመስግኗል፡፡ በዚሁ መሰረት ዩኒቨርሲው ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች እንዲሻገር ድጋፍ ላደረጉለት ሁሉ ጳጉሜን 4 ቀን 2012 ዓ. ም የምስጋና መርሃ ግብር በማዘጋጀት ለድጋፋቸው እውቅና ሰጥቷል፡፡ በሥነ ሥርዓቱ ላይ አቶ ጀማል አሊይ የአርሲ ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣ አቶ ገብሬ ኡርጌሶ የአሰላ ከተማ ከንቲባ፣ ዶ/ር ዱጉማ አዱኛ የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት፣ አባ ገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ሃዳ ሲንቄዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝትዋል፡፡

የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዱጉማ አዱኛ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ይህን መርሃ ግብር ማዘጋጀት ያስፈለገበት ምክንያት በተለያዩ መንገዶች ለዩኒቨርሲቲው ድጋፍ ላደረጉት አካላት ምስጋና ለማቅረብና እውቅና ለመስጠት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በዚህም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ከዩኒቨርሲቲው ጎን በመቆማቸው አመስግነዋል፡፡ በተለይም የጤና ባለሙያዎቻችን ለህይወታቸው ሳይሳሱ ወገኖቻችንን ከኮቪድ- 19 ለመታደግ በግንባር ቀደምነት መሰለፋቸው የሚያስመሰገናቸው ነው በማለት አመስገነዋል፡፡ የአርሲ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጀማል አሊይ በበኩላቸው ባሰሙት ንግግር መልካም ተግባራት የፈጸሙትን ማመስገን ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው አርሲ ዩኒቨርሲቲ ይህን መርሃ ግብር በማዘጋጀት መመስገን ያለባቸውን ማመስገኑ የሚያስመሰግነው ነው ብለዋል፡፡ የአሰላ ከተማ ከንቲባ አቶ ገብሬ ኡርጌሶ በበኩላቸው አርሲ ዩኒቨርሲቲ ለአሰላ ከተማ ነዋሪዎችና ለአካባቢው ማህበረሰብ ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው ወደ ፊትም ከከተማው አስተዳደር ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ በመግለጽ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት አባ ገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሃዳ ሲንቄዎች መርሃ ግብሩ መዘጋጀቱ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል፡፡ በመጨረሻም በጡረታ ለተገለሉ የቀድሞ ግብርና እና የአሰላ ሆስፒታል ሰራተኞችና ለአፎሚያ የአረጋውያን መርጃ ማህበር ለአመት በዓል መዋያ የሚሆኑ የምግብና የንጽህና መጠበቂያዎች ድጋፍ አድርገዋል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ለሚሰሩ የፀጥታ ሃይሎች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችና ሳኒታይዘር በስጦታ ተሰጥቷቸዋል፡፡ እንዲሁም ድጋፍ ላደረጉና እውቅና ለተሰጣቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ ድርጅቶች እና ታዋቂ ግለሰቦች የተዘጋጀው የምስጋና ምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡

Read 3289 times Last modified on Monday, 14 September 2020 17:34

Leave a comment

Make sure you enter all the required information, indicated by an asterisk (*). HTML code is not allowed.